hospital, patient, finger

የአንስቴዥያ ሙያ ከሌሎች የጤና ሙያዎች ባልተናነሰ ትኩረት እንደሚሻ ተነገረ።

የኢትዮጵያ አኒስቴትስቶች ማህበር ትናንት ታስቦ የዋለውን ዓለም አቀፍ የአንስቴዥያ ቀንን አስመልክቶ ነው ይህን የተናገረው።
ምንም እንኳ ካለፉት አስርት ዓመታት ወዲህ ለሙያው የተሻለ ትኩረት የተሰጠው ቢሆንም በቂ ግን አይደለም ብሏል ማህበሩ።
የማህበሩ ፕሬዝዳንትና በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሕክምና ትምህርት ቤት ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት አቶ ልዑልአየሁ አካሉ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ያላት የአንስቴትስቶች ብዛት ከ3000 አይበልጥም።
ይህ ደግሞ በዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው መስፈርት መሰረት ከሚያስፈለጓት ከ12,000 እስከ 15,000 የመስኩ ሙያተኞች አንፃር በጣም ዝቅተኛ ነው ተብሏል።
ስለሆነም ሙያተኞችን ለማፍራት ብርቱ ጥረትን ይጠይቃል መባሉን ሰምተናል።
በዚህ ረገድ መንግሥት ብርቱ ጥረት እያደረገ መሆኑን ማህበሩ ተናግሯል።
ከ10 ዓመት በፊት የአንስቴዢያ ትምህርት በ3 ዩንቨርስቲዎች ብቻ ይሰጥ እንደነበር ያስታወሱት በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የአንስቴዥያ መምህር እያያለም መለሰ ናቸው።
አሁን ግን ትምህርቱ በ27 ዩንቨርሲቲዎች እተሰጠ ነው ብለዋል።
ከእነዚህ መካከል በ7ቱ የአንስቴዥያ ትምህርት በሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ ይሰጥባቸዋል።
ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ የትምህርቱ ከሁለተኛ ዲግሪ በላይ አለመሰጠት ብዙዎች ከአንስቴትስትነት በመኮብለል ተዛማጅ የሙያ መስኮችን ይቀላቀላሉ ተብሏል።
ይህ ደግሞ የባለሙያዎቹን ጥረት በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዳያደርገው አስግቶናል ብለዋል የኢትዮጵያ አንስቴትስቶች ማህበር የስራ ኃላፊዎች።
በመሆኑም የሚመለከታቸው አካላት ትምህርቱ በሶስተኛ ዲግሪ ማለትም በዶክትሬት ዲግሪ ደረጃ እንዲሰጥ እንዲሰሩም ጠይቀዋል።
ሙያውን ለማሳደግና ሙያተኛውንም ለማቆየት ሁነኛ መላ እንደሆነም ነው የተናገሩት።
አንስቴቲስቶች በሌሉበት የቀዶ ሕክምና አገልግሎት መስጠት የማይታሰብ መሆኑን አንስተው ለመስኩ ተገቢ የሆነ ትኩረት እንዲሰጠው መክረዋል። 174ኛው ዓለም አቀፍ የአንስቴዥያ ቀን ታናንት ታስቦ ውሏል።
የኢትዮጵያ አንስቴትስቶች ማህበርም በኮቪድ 19 ወቅት ደረጃውን የጠበቀ እና በእኩል ተደራሽ የሆነ የአንስቴዥያ አገልግሎት ለሕብረተሰቡ ማድረስ በሚል መሪ ቃል እለቱን አስቦ ውሏል።
በየነ ወልዴ
%d bloggers like this: