175ኛው አለም አቀፍ የአንስቲዥያን ቀን

በበዓሉ የጤና ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች፣ የአንስቴቲስቶች ማህበር ሃላፊዎችና አባላት፣ የአዲስአበባ ዩኒቨርሲቲ የአንስቲዥያ ትምህርት ክፍል ተማሪዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆኑ የተሰሩ ስራዎችን የሚያሳይ አውደ ርእይ፣ የደም ልገሳ መርሃ ግብር እና የፓናል ውይይት እንዲሁም ሌሎች ተግባራትን በማከናወን ነው በዓሉ የተከበረው፡፡

በኮቪዲ ምክንያት ህይወታቸው ላለፈ ሙያተኞችም የህሊና ጸሎት ተደርጓል፡፡የጤና ሚኒስቴር ሰው ሃይል ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አሰግድ ሳሙኤል አንስቲዥያ በቀዶ ጥገና ህክምና ጊዜ ታካሚዎች ምቹ ሆነው አገልግሎት እንዲያገኙ የቀዶ ጥገና ባለሙያውም ተረጋግቶ የሚጠበቀውን አገልግሎት ከመስጠት አንጻር ትልቅ ሚና ያለው ሙያ መሆኑን የገለጹ ሲሆን ባለፉት 10 ዓመታት የጤና ሚኒስቴር የጤና ባለሙያዎችን ቁጥር ለመጨመር በርካታ ስራዎችን ሲሰራ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ የባለሙያ ከፍተኛ እጥረት የነበረበት የጤና ሙያ አንዱ የአንስቲዥያ ሙያ እንደሆነ አስታውሰው ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገው ከፍተኛ ርብርብ የሙያተኛ ቁጥሩን መጨመር መቻሉን የገለጹ ሲሆን በቀጣይም የጤና ባለሙያው የበለጠ ተነሳሽ፣ ብቁ፣ ርህሩህ ሆኖ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያስችሉ ስራዎች በስፋት ከማህበሩ ጋር ይሰራል ብለዋል፡፡ የተከታታይ የሙያ ማጎልበቻ ስርዓትም በስፋት እየተሄደበት መሆኑ ገልጸዋል፡፡ የጤና ዘርፍ አገልግሎት በቡድን የሚሰራ እንደመሆኑ መጠን ከሁሉም ባለሙያዎች ጋራ በትብብር እንዲሰራ የሚያስችል የስራ አካባቢ መፍጠር እንዲቻልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በመጨረሻም በመላው ኢትዮጵያ ላሉ የአንስቲዥያ ሙያተኞች እያደረጉ ላሉት አገልግሎት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ የአንስቴቲስቶች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ልኡልአየሁ አካሉ በበኩላቸው እለቱ ለመጀመሪ ጊዜ ታካሚዎች ምንም አይነት ህመም ሳይሰማቸው ቀዶ ጥገና ተደርገው ተፈውሰው የወጡበት ቀንን ምክንያት በማድረግ የሚከበር እለት እንደሆነ አንስተው ለአንስቲዥያ ሙያ መገኘት መሰረት የሆነ ቀን መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ይህ በዓል ለማክበር የጤና ሚኒስቴር ከማህበሩ ጎን ሆኖ ድጋፍ እንዳደረገላቸው የገለጹት ፕሬዝዳንቱ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በተከታታይ የሙያ ማጎልበቻ፣ በብቃት ምዘና፣ በኮቪድ መከላከል፣ ብቁና ርሁሩህ ባለሙያ በማፍጠር ረገድ ዘርፍ ብዙ ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝ አክለው ገልጸዋል፡፡ፕሬዝዳንቱ የኢትዮጵያ የአንስቴቲስቶች ማህበር በመላው አገሪቱ እየተንቀሳቀሰ በክልሎች የቅርጫፍ ጽ/ቤት ከፍቶ ሙያተኞችን ተደራሽ በማድረግ ጥራቱን የጠበቀ የአንስቲዥያ አገልግሎት እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸው የአንስዥያ ትምህርትን በስርዓተ ትምህርት የመከለስ፣ ለመምህራን የሙያ ማበልጸጊያ ስልጠና የመስጠት እና በዩኒቨርሲቲዎች አቅም የመገንባት ስራዎችም እየተሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

%d bloggers like this: